የዞራስተር ፍካሬ: ወደ ሁሉምና ወደ ማንም በፍሬድሪች ዊልሄልም ኒሺ የተደረሰ የፍልስፍና ልቦለድ* ነው። መጽሐፉ በ1883 እና 1885 (እ.ኤ.አ) መካከል በ4 ክፍል የተደረሰ ሲሆን በጊዜው ይሰራበት ከነበረው የአስተሳሰብ ዘዴ ለየት ባለ መልኩ የፍልስፍናን እና የግብረገብን ጥናቶች መርምሯል። የመጽሃፉ አትኩሮቶች፡- የዘላለማዊ ምልልስ፣ ኃይልን መፍቀድ (*ፈቃድ እዚህ ላይ ጠንካራ ፍላጎት ማለት ነው)፣ የአምላክ በጊዜው በነበሩ አውሮጳውያን ልብ ውስጥ መሞት፣ ስለዚህም የአዳዲስ ዋጋ ወይም ህግጋት አስፈላጊነት፣የበላይ ሰው (*በኒሺ አስተሳሰብ የሰው ልጅ በጦጣዎችና በበላይ ሰው መካከል ያለ ፍጡር ነው) መምጣት ትምህርቶች ነበሩ። ጽሁፉ የመጽሐፍ ቅዱስ አጻጻፍ ስልት ይከተል እንጂ የውስጡ ፍሬ ነገር ግን የክርስትናና አይሁድ ሃይማኖቶችን መሰረታዊ እምነቶች የሚጻረር ነበር። ኒሺ ይህን መጽሐፍ ከሰዎችና ከጊዜ 6000 ጫማ እርቆ እንደጻፈ ይናገራል፣ ማለቱም የመጽሃፉን ሃሳቦች በተራራ ላይ እያለ እንዳገኛቸው ለማስገንዘብ ነበር።
ኒሺ "የዞራስተር ፍካሬ" ብሎ የሰየመውን መጽሃፍ "ስርዓት አልባ"(ጥራዝ ነጠቅ) በሆነ ዘዴ ስለጻፈው ለተመራማሪወች እጅግ አስቸጋሪ ሆነ። ይሁንና ተመራማሪወች አንድ አንድ ቋሚ የሆኑ የመጽሃፉን ይዘቶች ማስተዋላቸው አልቀረም፦
በመጽሃፉ መግቢያ ላይ ዞራስተር 30 አመት ሲሞላው ወደ ተራራ እንደወጣና በዚያ ከሰወች ተለይቶ ብዙ ጥበቦችን እንደሰበሰብ እናነባለን። 40 አመት ሲሞላው ያከማቸውን ጥበብ ለማካፈል ከተራራው ወረደ። የመውረዱ ዋና አላማ "የበላይ ሰው"ን መምጣት ለመስበክ ነበር። የበላይ ሰው፣ በዞራስተር አስተሳሰብ፣ ከሰው በላይ የሆነ ፍጡር ማለት ነው፡ ልክ የሰው ልጅ ከጦጣወች በላይ የሆነ ፍጡር እንደሆነ።
በዞራስተር ግምት ዘመናዊው ሰው የወኔ ግሽበት፣ ባዶነትና አጠቃላይ የህይወት ውዥንብር ስለገጠመው አዲስ ትምህርት ያስፈልገዋል። በዞራስተር አስተሳሰብ የዘመናዊው ሰው መንፈሳዊ ግሽበት ምክንያት የአምላክ መሞት ነው። በርግጥ አምላክ ለመሞት አይቻለውም ሆኖም ግን በዞራስቶር አስተሳሰብ አምላክ ሞተ ማለቱ ዘመናዊው ሰው በአምላክ ላይ ያለው እምነቱ ሞተ ማለት ነው። ስለሆነም የድሮወቹ ሰወች ብዙ አስደናቂ ስራወችን ለአምላክ ሲሉ ቢሰሩም የዘመናዊው ሰው ግን ይህን እመንቱን በማጣቱ አጠቃላይ ዘመናዊ ህብረተሰብ መሪ ሃሳብ የማጣት፣ የመበስበስና ተስፋ የማጣት ምልክቶች አሳየ። ህግን የሚሰጥ በሰው አምሳያ ያለ አምላክ ለአዲሱ ሳይንሳዊና ዘምናዊ ህብረተሰብ እጅግ ኋላ ቀር መስሎ ታየ። ስለሆነም በተለይ በተማሩ ሰወች ዘንድ የአለም የህይወት ትርጉምና የግብረገብ ስርዓት እጅግ ዝብርቅርቅ ያለ ሆነ። ዘመናዊ ሰው ባዶነት "ኒሂልዝም"( የህይወት ትርጉም ማጣት) የሚባል ችግር ተጋረጠው፣ "የዞራስተር ፍካሬ" ዋና አላማ ይህን ባዶነት መታገል ነበር። በኒሺ አስተሳሰብ አዲሱ የ"በላይ ሰው" ትምህርት ለዚህ ዘመናዊ ኒሂሊዝም (ባዶነት) ፍቱን መድሃኒት መሆን ነበር።
ዞራስተር ከተራራው ወርዶ በሰወች መካከል እንዲህ ሲል ሰበከ፡ የሰው ልጅ በአሁኑ ሰዓት ያለበትን መናኛነት (ተራነት)ና የከሰረ ስልጣኔ በማሸነፍ የ"በላይ ሰው"ን መፍጠር አለበት፡ «የሰው ልጅ ሊሸነፍ የሚገባ ነው። ለማሸነፍ እያንዳንዳችሁ ምን አድርጋችኋል?» ሆኖም ግን ይህ ሰበካው ተቀባይነት አጣ። ህዝቡም መልሶ «የበላይ ሰውህን እዚያው ለራስህ» ብለውም ተሳለቁበት። የተመቻቸና ጥሩ ኑሮ ከመፈለግ ውጭ የበላይ ሰውን እንደማይፈልጉ ነገሩት። ህይወት የበለጠ ትርጉም ካልተሰጠው በርግጥም ከደስታ ውጭ ምንስ ያስፈልጋል? በዚህ ምክንያት የስልጣኔ ዋና ዓላማ ተራ መናኛ ሆነ፣ እርሱም፡- "ከፍተኛ ደስታ ለከፍተኛ ቁጥር ላለው ሰው" ሆነ።
ይህ ተራነት ዞራስተር ለህዝቡ ያለው ጥላቻና ንቀት እንዲያድግ አደርገ ( ምንም እንኳ ከጊዜ ወደጊዜ ሊያዝንላቸውና ሊረዳቸው ህሊናው ቢግደረደርም)። ተማሪውም ሆነ ያልተማረው፣ ፖለቲከኛውም ሆነ ፈላስፋው፣ ሰዓሊውም ሆነ ፕሮፌሰሩ፣ ሁሉም የተደላደለ ህይወት ከመሻት ውጭ ውስጣቸው ያለውን እምቅ ስብዕና ለማሳደግ የማይጥሩ ሆኖ አገኛቸው። ካደረበት ንቀት የተነሳ ዞራስተር ብዙ ተከታይ ከማፍራት ይልቅ ሊግባባቸው የሚችሉ ጥቂት ፈርጥ የሆኑ ሰወችን ፍለጋ ጀመረ፡ ተራ(መናኛ) ነገሮችን ከህይወት ለማግኘት የሚሞክሩን ሳይሆን፣ ከፍተኛ ነገርን ለማግኘት የሚሞክሩትን። ፍለጋው ጥቂት ሰወችን ስላስገኘለት ለኒህ ለተመረጡት "ማስተማር" በጥብቅ ጀመረ።
የመጨረሻው የመጽሃፉ እትም 4 ክፍሎች አሉት። እያንዳንዱ ክፍል ለማብራራት ብዙ ቦታ ስለሚይዝ ከዚህ በታች በየራሳቸው ገጽ ማብራሪያቸው ሰፍሯል። ይመልከቱ።
ዋና መጣጥፍ፦ የዞራስተር ፍካሬ ክፍል ፩
ዋና መጣጥፍ፦ የዞራስተር ፍካሬ ክፍል ፪
ዋና መጣጥፍ፦ የዞራስተር ፍካሬ ክፍል ፫
ዋና መጣጥፍ፦ የዞራስተር ፍካሬ ክፍል ፬
This article uses material from the Wikipedia አማርኛ article የዞራስተር ፍካሬ, which is released under the Creative Commons Attribution-ShareAlike 3.0 license ("CC BY-SA 3.0"); additional terms may apply (view authors). Content is available under CC BY-SA 4.0 unless otherwise noted. Images, videos and audio are available under their respective licenses.
®Wikipedia is a registered trademark of the Wiki Foundation, Inc. Wiki አማርኛ (DUHOCTRUNGQUOC.VN) is an independent company and has no affiliation with Wiki Foundation.