ግድብ ማለት ከመሬት ስር ያለንም ሆነ ከመሬት ላይ (ሸለቆ ውስጥ) የሚፈስን ውሃ ገድቦ ወይንም አንቆ የሚይዝና ሰው ሰራሽ ሃይቅ ለመፍጠር የሚረዳ እንቅፋት ነው። በጐንና በጐን የሚገኙት ሸለቆዎችም የግድቡ አካል ሲሆኑ የሃይቁን የጎንዮሽ ዳርቻዎችን ይወስናሉ። ግድብ የሚለው ቃል የግድብ አካል የሆኑ የግንባታ ክፍሎችን ማለትም እንቅፋት ፈጣሪውን አካል፣ ውሃ የታቆረበትን አካባቢ፣ ውሃውን ለመጠቀም የሚረዱ ግንባታዎችን እንዲሁም የውሃ መጠንን ለመቆጣጠር የሚረዱ ግንባታዎችን ያጠቃልላል። ግድብን ከውሃ መጠን መቆጣጠሪያ (ዊር) የሚለየው ሙሉ በሙሉ ሸለቆውን እንዲዘጋ ተደርጐ የሚገነባ በመሆኑ ነው።
ግድቦች ለሚከተሉት አገልግሎቶች ሊውሉ ይችላሉ
የግድብን የማጠራቀም ችሎታ ግድቡ ማቆር የሚችለውን መጠን በአመት ውስጥ ወደ ግድቡ ለሚፈሰው የውሃ መጠን በማካፈል መመዘን ይቻላል። ጥሩ የማጠራቀም ችሎታ ያላቸው ግድቦች የማጠራቀም ችሎታ 1 (100%) ነው። የውሃ መጥለቅለቅ ችግርን ለመቅረፍና የወንዞችን ከፍታ ለመጨመር ለሚሠሩ ግድቦች 0.3 (30%) የማጠራቀም ችሎታ በቂ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።
ግድቦች በብዙ መንገድ ተሰርተው ይገኛሉ፣ ለምሳሌ በሰው ልጅ አቅድ፣ ወይንም ደግሞ እንዲሁ በተፈጥሮ ሂደት፣ አልፎ አልፎ ደግሞ በዱር አራዊት፣ ለምሳሌ በድብ ተሰርተው ይገኛሉ። ሰው ሠራሽ ግድቦች በመጠናቸው (በቁመታቸው)፣ በተሠሩበት አላማ እና በአወቃቀራቸው ከፋፍሎ ማየት ይቻላል።
ሰው ሠራሽ የግድብ ዓይነቶች ከመዋቅር አንጻር፡
ግስበት ግድብ ባለው ግዙፍነት ምክንያት የመሬት ስበትን በመጠቀም የውሃን ሃይልና ሌሎች ጫናዎችን ተቋቁሞ የሚቆም የግድብ አይነት ነው። የድልዳሎ ግድቦችና ከብደት ያላቸው የግንብ ግድቦች ዋነኞቹ የግስበት ግድብ አይነቶች ናቸው።
የድልዳሎ ግድቦች ከአፈር እና ከድንጋይ ተደልድለው የሚሠሩ ግድቦች ናቸው። የድልዳሎ ግድቦች በክብደታቸውና ዝቅተኛ ተዳፋትነት ባላቸው ጐኖቻቸው አማካኝነት ሚዛናቸውን ይጠብቃሉ። የድልዳሎ ግድቦች መሀላቸው ወይም በውሃ አቅጣጫ ያለው ውጫዊ አካላቸው ውሃ እንዳያሰርግ ተደርገው ይገነባሉ።
ውጫዊ የስርገት መከላከያ በሚጠራቀመው ውሃ አቅጣጫ ከግድቡ የጎን ውጫዊ አካል ላይ ከሸክላ አፈር ወይም ከአስፋልት የሚሰራ የግድቡ አካል ነው። ውጫዊ የስርገት መከላከያ በአየር መፈራረቅና በውሃ ማዕበል ምክንያት ለሚመጡ ጉዳቶች ተጋላጭ ስለሆነ ጥቅም ላይ በሚውልበት ጊዜ እነዚህን ተቃርኖዎች ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል።
ውስጣዊ የስርገት መከላከያ በግድቡ መሀል በአብዛኛው ከሸክላ አፈር የሚሠራ ሲሆን የግንባታ ስራው ከተጠናቀቀ በኋላ የእድሳት ወይም የማሻሻል ሥራ ለማድረግ በጣም ከባድ ነው። ከዚህም በተጨማሪ የውሃው ግፊት የሚያርፈው በቀጥታ በስርገት መከላከያው ላይ ስለሆነ የውሃ ግፊቱን ለመቋቋም የሚረዳው የግድቡ አካል ከስርገት መከላከያው ጀርባ ያለው የግድቡ ክፍል ብቻ ይሆናል። በዚህም ምክንያት ውጫዊ የስርገት መከላከያ ካላቸው ግድቦች ጋር ሲነፃፀር የውስጣዊ ስርገት መከላከያ ያላቸው ግድቦች መጠን (ግዝፈት) ትልቅ ሲሆን ለግንባታ የሚያስፈልገው ቁስ መጠንም ብዛት ያለው ነው።
የግንብ ግድቦች ከግስበት ግድቦች የሚመደቡ ሲሆን ከኮንክሪት ?? ወይም ከሲሚንቶና አሸዋ ድብልቅ (ሞርታር) በተያያዙ ድንጋዮች የሚሰሩ ናቸው። የግንብ ግድቦች ቅርፅ በአመዛኙ ሶስት ማዕዘናማ አይነት ሲሆን በውሃ በኩል ያለው ጎን ወደ ቀጥታ ያመዘነ ሆኖ ከውሃው በተቃራኒ በኩል ያለው ጐን በአንፃሩ ያጋደለ ነው። የግንብ ግድቦች የታች ስፋት ከቁመታቸው ጋር ሲነፃፀር 2 ለ 3 የሆነ ምጥጥን ሲኖረው ወደ አናታቸው ሲሄድ ስፋታቸው እየቀነሰ ሄዶ አናቱ ላይ ለመኪና መጒጒዋዣ ያህል ሊሆን የሚችል ስፋት አላቸው።
ቅስት ግድብ ከቅስት የሚሰራ ሲሆን የሚያቁረውን ውሃ ሃይል የሚቋቋመው ከቅስቱ ጉልበት የመቋቋም ባህርይ ተነስቶ ነው።
ብዙ በሮች ያሉት የግድብ አይነት ሲሆን በሮቹን በመክፈትና በመዝጋት በውስጡ የሚያልፍን የውሃ መጠን ለመቆጣጠር የሚያገለግል የግድብ አይነት ነው። ለመስኖ ስራ ያገልግላል።
ሰው ሠራሽ የግድብ ዓይነቶች ከጥቅም አንጻር፡
የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድቦች 19% የአለምን የኤሌክትሪክ ፍላጎት ያሟላሉ። ታዳሽ ከሚባሉት የኤሌክትሪክ ማመንጫዎች ደግሞ 68% ይይዛሉ።
This article uses material from the Wikipedia አማርኛ article ግድብ, which is released under the Creative Commons Attribution-ShareAlike 3.0 license ("CC BY-SA 3.0"); additional terms may apply (view authors). Content is available under CC BY-SA 4.0 unless otherwise noted. Images, videos and audio are available under their respective licenses.
®Wikipedia is a registered trademark of the Wiki Foundation, Inc. Wiki አማርኛ (DUHOCTRUNGQUOC.VN) is an independent company and has no affiliation with Wiki Foundation.