ግዕዝ ፡ በአፍሪካ ቀንድ ፡ በኢትዮጵያና ፡ በኤርትራ ፡ በጥንት ፡ የተመሠረተና ፡ ሲያገለግል ፡ የቆየ ፡ ቋንቋ ነው። የግዕዝ ፡ አመጣጥ ፡ በግምት ፡ የዛሬ ፡ ፫ ፡ ሺህ ፡ ዓመት ፡ ከየመን ፡ እና ፡ ደቡብ ፡ አረቢያ ፡ በመነሣትና ፡ ቀይ ፡ ባሕርን ፡ በመሻገር ፡ በኤርትራ ፡ እና፡ ሰሜን ፡ ኢትዮጵያ ፡ ውስጥ ፡ ከሰፈሩ ፡ የተለያዩ ፡ የሳባውያን ፡ ነገዶች ፡ ቋንቋና ፡ በጊዜው ፡ ሰሜን ፡ ኢትዮጵያ ፡ ይነገሩ ፡ በነበሩ ፡ ቋንቋዎች ፡ ዘገምተኛ ፡ ውኅደት ፡ ነው። በአክሱም ፡ መንግሥትና ፡ በኢትዮጵያ ፡ መንግሥት ፡ መደበኛ ፡ ቋንቋ ፡ ነበር።
ግዕዝ ፡ ከአማርኛና ፡ ሌሎች ፡ ኢትዮ-ሴማዊ ፡ ቋንቋዎች ፡ ጋር ፡ ሲወዳደር ፡ «ንጹሕ» ፡ ሴማዊ ፡ ቋንቋ ፡ ነው። ግዕዝ ፡ እስከ ፡ ፲ኛው ፡ ክፍለ-ዘመን ፡ መጀመሪያ ፡ ድረስ ፡ ዋነኛ ፡ የመግባቢያ ፡ ቋንቋና ፡ ልሳነ ፡ ንጉሥ ፡ ነበር። ከ ፲፫ኛው ፡ ክፍለ ፡ ዘመን ፡ ጀምሮ ፡ ግን ፡ ሙሉ ፡ በሙሉ ፡ መነገር ፡ አቁሞ ፡ በሰሜን ፡ ኢትዮጵያ ፡ በትግርኛ ፡ እንዲሁም ፡ በማዕከላዊው ፡ ክፍል ፡ ደግሞ ፡ በአማርኛ ፡ ተተካ። ዛሬ ፡ በኢትዮጵያ ፡ ኦርቶዶክስ ፡ ተዋሕዶ ፡ ቤተክርስቲያን ፡ ሥነ-ስርዓት ፡ እንዲሁም ፡ በኤርትራ ፡ ኦርቶዶክስ ፡ ተዋሕዶ ፡ ቤተክርስቲያን ፣ በኢትዮጵያ ፡ ካቶሊክ ፡ ቤተክርስቲያን እና ፡ በቤተ-እስራኤል ፡ ሥነ-ስርዓቶች ፡ ይሰማል። በሰሜን፡ ኤርትራ ፡ የሚገኘ ፡ ትግረ ፡ የሚባል ፡ ቋንቋ ፡ ከሁላቸዉ፡ የሰሜን ፡ኢትዮጵያ ፡ቋንቋዎች፡ ለግእዝ ፡ በቅርብ ፡ ይዛመዳል ፡ እና። ትግረ ፡ ፸ በመቶ ፡ ግእዝ ፡ ነዉ ፡ እና ፡ በመቀጠል ፡ ትግርኛ ፡ እና ኣማርኛ።
ቋንቋው ፡ የሴማዊ ፡ ቋንቋዎች ፡ አባል ፡ እየሆነ ፡ በደቡብ ፡ ሴማዊ ፡ ቅርንጫፍ ፡ ውስጥ ፡ ይካተታል። ደቡብ ፡ ሴማዊ ፡ በመባሉ ፡ ግዕዝ ፡ የሣባ ፡ ቋንቋ ፡ ቅርብ ፡ ዘመድ ፡ ነው። ግዕዝ ፡ የተጻፈው ፡ በግዕዝ ፡ ፊደል ፡ አቡጊዳ ፡ ነው። ይህም ፡ ፊደል ፡ ደግሞ ፡ ዛሬ ፡ ለአማርኛ ፣ ለትግርኛ ፡ እና ፡ ለሌሎችም ፡ ቋንቋዎች ፡ ይጠቀማል። በመላውም ፡ የአፍሪቃ ፡ አህጉር ፡ ውስጥ ፡ የመጀመሪያውና ፡ ብቸኛ ፡ አፍሪቃዊ ፡ የራሱን ፡ ፊደላት ፡ የያዘ ፡ ቋንቋ ፡ ሲሆን ፣ በዓለምም ፡ ላይ ፡ ዋናና ፡ የስልጣኔ ፡ አራማጅ ፡ ከሚባሉት ፡ ቋንቋዎች ፡ አንዱ ፡ ነው።
በግዕዝ ፡ ጽሕፈት ፡ ፳፮ ፡ ፊደላት ፡ ብቻ ፡ ይጠቀሙ ፡ ነበር ፤ እነርሱም፦
ሀ ፣ ለ ፣ ሐ ፣ መ ፣ ሠ ፣ ረ ፣ ሰ ፣ ቀ ፣ በ ፣ ተ ፣ ኀ ፣ ነ ፣ አ ፣ ከ ፣ ወ ፣ ዐ ፣ ዘ ፣ የ ፣ ደ ፣ ገ ፣ ጠ ፣ ጰ ፣ ጸ ፣ ፀ ፣ ፈ ፣ ፐ
ናቸው።
ሊቁ ፡ ሪቻርድ ፓንኩርስት ፡ እንደሚጽፍ ፣ አንድ ፡ ተማሪ ፡ በመጀመርያው ፡ አመት ፡ ፊደሉን ፡ ከተማረ ፡ በኋለ ፣ በሚከተለው ፡ አመት ፡ መጀመሪያይቱ ፡ የሐዋርያው ፡ የዮሐንስ ፡ መልእክትን ፡ ከአዲስ ፡ ኪዳን ፡ በግዕዝ ፡ ከትዝታ ፡ ለመጻፍ ፡ መማር ፡ ነበረበት። በሦስተኛው ፡ ደረጃ ፡ የሐዋርያት ፡ ሥራ ፡ በአራተኛውም ፡ መዝሙረ ፡ ዳዊት ፡ በግዕዝ ፡ ማስታወስ ፡ ነበረበት። ይህንን ፡ ከጨረሰ ፡ ታላቅ ፡ ግብዣ ፡ ይደረግና ፡ ልጁ ፡ ጸሐፊ ፡ ይሆን ፡ ነበር።
በብሪቲሽ ፡ ቤተ-መጻሕፍት ፡ (የእንግሊዝ ፡ አገር ፡ ብሔራዊ ፡ ቤተ-መጻሕፍት) ፡ ውስጥ ፡ ፰፻ ፡ የሚያሕሉ ፡ የድሮ ፡ ግዕዝ ፡ ብራናዎች ፡ አሉ።
በኢ.ኦ.ተ.ቤ. ፡ ትምህርቶች ፡ ዘንድ ፣ ግዕዝ ፡ የአዳምና ፡ የሕይዋን ፡ ቋንቋ ፡ ነበር። ፊደሉን ፡ የፈጠረው ፡ ከማየ አይኅ ፡ አስቀድሞ ፡ የሴት ፡ ልጅ ፡ ሄኖስ ፡ ነበረ። ከባቢሎን ፡ ግንብ ፡ ውድቀት ፡ በኳላ ፣ ከአርፋክስድ ፡ ወገን ፡ የዮቅጣን ፡ ልጆች ፡ ቋንቋውን ፡ እንደ ፡ ጠበቁት ፡ ይባላል። የዮቅጣን ፡ ልጅ ፡ ሣባ ፡ ነገዶች ፡ ከዚያ ፡ ቀይ ፡ ባሕርን ፡ አሻግረው ፡ ወደ ፡ ዛሬው ፡ ኢትዮጵያ ፡ ያስገቡት ፡ ይታመናል። እንዲሁም ፡ ካዕብ ፡ እስከ ፡ ሳብዕ ፡ (አናባቢዎችን ፡ ለመለየት) ፡ ወደ ፡ ፊደል ፡ የተጨመረበት ፡ ወቅት ፡ በንጉሥ ፡ ኤዛና ፡ ዘመን ፡ እንደ ፡ ነበር ፡ ይባላል።
የቱ
«ቃለ ፡ በረከት ፡ ዘሄኖክ ፡ ዘከመ ፡ ባረከ ፡ ኅሩያነ ፡ ወጻድቃነ ፡ እለ፡ ሀለው፡ ይኩኑ ፡ በዕለተ ፡ ምንዳቤ ፡ ለአሰስሎ ፡ ኲሉ ፡ እኩያን ፡ ወረሲዓን።» (መጽሐፈ ፡ ሄኖክ ፩ ፡ ፩)
ሄኖክ ፡ መጀመርያ ፡ ቃሎች ፡ በጽሕፈት ፡ በግዕዝ ፡ የጻፈ ፡ እንደ ፡ ነበር ፡ ስለሚባል ፣ ይህ ፡ ቃል ፡ በማንኛውም ፡ የሰው ፡ ልጅ ፡ ቋንቋ ፡ ከሁሉ ፡ አስቀድሞ ፡ የተጻፈ ፡ መሆኑ ፡ በብዙዎች ፡ የኢትዮጵያ ፡ ሊቃውንት ፡ ይታመናል።
This article uses material from the Wikipedia አማርኛ article ግዕዝ, which is released under the Creative Commons Attribution-ShareAlike 3.0 license ("CC BY-SA 3.0"); additional terms may apply (view authors). Content is available under CC BY-SA 4.0 unless otherwise noted. Images, videos and audio are available under their respective licenses.
®Wikipedia is a registered trademark of the Wiki Foundation, Inc. Wiki አማርኛ (DUHOCTRUNGQUOC.VN) is an independent company and has no affiliation with Wiki Foundation.